የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች በኢትዮጵያ ከሚገኙ አስራአንድ ክልሎች አንዱ ነው። 105,887.18 ካሬ ኪ.ሜ. ቦታ የሚሸፍን ሲሆን[1] በምዕራብ በጋምቤላ፣ በደቡብ ምዕራብ ከደቡብ ሱዳን፣ ሰሜን ምሥራቅና ደቡብ ምሥራቅ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ከኬንያ ጋር ይዋሰናል።[2] የክልሉ ዋና ከተማ ሃዋሳ ሲሆን ሌሎች ትልቅ ከተማዎች ወልቂጤ፣ ጉብርየ፣ አርባ ምንጭ፣ ሆሳዕና፣ቡታጂራ፣ ክብረመንግሥት፣ ያቤሎ፣ አላባ፣ አገረሠላም፣ አለታዎንዶ፣ ቦዲቲ፣ ወንዶ፣ ዲላ፣ ይርጋለም፣ ጂንካ፣ ሶዶ፣ ቦንጋ፣ ሚዛን ተፈሪ ናቸው።
ክልሉ በ፲፫ ዞኖችና ፰ ልዩ ወረዳዎች በ፳፪ የከተማ አስተዳደሮች የተደራጀ ሲሆን በ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. በተደረገው የሕዝብና ቤት ቆጠራ መሠረት 15,042,531 ሕዝብ የሚገኝበት ሲሆን ይህም ከአገሪቱ ጠቅላላ ሕዝብ 20.4% ይሸፍናል።[2] ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ ፶፮ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የሚኖሩ ሲሆን የእነዚህም ቋንቋዎች በአፍሮ እስያዊ (ኩሻዊ፣ ኦሞአዊ እና ሴማዊ ንዑስ ክፍሎችን ጨምሮ) እና ናይሎ ሳህራዊ የቋንቋ ቤተሰቦች ይመደባሉ።[2]