ከውጭ የሚገቡም ሆነ በሀገር ውስጥ የሚመረቱ የኤሌክትሪክ የሕዝብ ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች፣ የቤት አውቶሞቢሎች እና የዕቃ መጫኛ ተሽከርካሪዎች ላይ ዝቅተኛ የጉምሩክ ታሪፍ እንደሚጣልባቸው እና ከተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ከኤክሳይዝ ታክስ እና ከሱር ታክስ ነፃ እንደተደረጉ የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የገንዘብ ሚኒስቴር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ኢንቨስትመንት ላይ የሚሰማሩ ኢንዱስትሪዎችን እና አስመጪዎችን የሚያበረታታ እንዲሁም ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርግ የታክስ ማሻሻያ ተግባራዊ መደረጉን አስታውቋል።

የታክስ ማሻሻያው ዓላማ በአገራችን በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ የመጣውን የተሽከርካሪዎች ቁጥር በፖሊሲ ማዕቀፍ ከአካባቢ ደህንነት ጋር የሚስማማ ለማድረግ፣ በኅብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት የማያስከትል፣ በአየር ንብረትና በብዝሃ ህይወት ላይ ተጽእኖ የማያሳርፍ እና ታዳሽ የኃይል ምንጮችን በአግባቡ የሚጠቀም የመጓጓዣ ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ ሲሆን የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ እንዲቀርቡ ለማስቻልም ነው።

በታክስ ማሻሻያው መሰረት የኤሌክትሪክ የቤት አውቶሞቢሎችን በተመለከተም ሙሉ በሙሉ ተበትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ አውቶሞቢሎች ከጉምሩክ ቀረጥ፣ ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል።

በከፊል ተበትነው ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው የሚገጣጠሙ የኤሌክትሪክ የቤት አውቶሞቢሎችን በተመለከተም 5 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ብቻ የሚጣልባቸው ሲሆን ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ ተደርጓል።

ሙሉ ለሙሉ ተገጣጥመው ያለቀላቸው የኤሌክትሪክ አውቶሞቢሎች ወደ ሀገር ሲገቡ ደግሞ 15 በመቶ የጉምሩክ ቀረጥ ብቻ የሚጣልባቸው ሲሆን ከኤክሳይዝ ታክስ፣ ከተጨማሪ እሴት ታክስና ከሱር ታክስ ሙሉ በሙሉ ነጻ እንዲሆኑ መወሰኑን ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

Leave a Reply

Required fields are marked *